Right to work in the UK

በዩኬ ውስጥ የመስራት መብት

የእንግሊዝ ዜጋ ካልሆኑ በስተቀር፣ ዩኬ ውስጥ የመስራት መብት እንዳልዎት ማረጋገጥ የሚጠበቅብዎ ሲሆን ቀጣሪዎች አንድን ሰው በህገወጥ መንገድ ቀጥረው ቢገኙ የገንዘብ ቅጣት ሊቀጡ ወይም በእስር ሊቀጡ ይችላሉ። ዩኬ ውስጥ ከ 20 በላይ አይነት ልዩ የስራ ፍቃዶች ያሉ ሲሆን ዝርዝሩ በመደበኛነት ማሻሻያ ይደረግበታል። ዩኬ ውስጥ ለመስራት የሚያስችልዎ ትክክለኛው ቪዛ ያልዎት መሆኑን ለማወቅ ይህን የኦንላይን አገልግሎት ይጠቀሙ።

 

የመስራት መብትን ማረጋገጥ

የስደተኝነት ደረጃዎን በኦንላይን ማየት እንደሚችሉ ከተነገርዎ በዩኬ ውስጥ የመስራት መብትዎን ለማረጋገጥ የማጋሪያ ኮድ ማግኘት ይችላሉ። ኮዱ የሚያገለግለው ለ 30 ቀናት ሆኖ ለቀጣሪዎች ሊጋራ የሚችል ሲሆን እነርሱም የሚከተሉትን ሊያረጋግጡ ይችላሉ:

  •  ለመስራት የተፈቀደልዎትን የስራ አይነት
  •  ዩኬ ውስጥ ለምን ያክል ጊዜ ርዝመት መስራት እንደሚችሉ
  •  ጥቅማ ጥቅሞች መጠየቅ የሚችሉ ወይም የ NHS አገልግሎቶችን የሚያገኙ ስለመሆኑ
  •  የባንክ ሂሳብ መክፈት ስለመቻልዎ

የማጋሪያ ኮድዎን በ መንግስት ድረገጽ በኩል ማግኘት ይችላሉ። ፓስፖርትዎ ወይም የመታወቂያ ካርድዎ፣ የባዮሜትሬክ/አሻራ የመኖሪያ ፍቃድ(BRP) ወይም ቪዛ እና የባዮሜትሪክ የነዋሪነት ካርድ ቁጥር ያስፈልግዎታል።

 

ብሔራዊ የመድን ዋስትና ቁጥር ምንድን ነው?

NINO የብሔራዊ መድን ዋስትና ቁጥርን የሚወክል ሲሆን ግብር እና ለብሔራዊ መድን ዋስትና ለመክፈል እና ጥቅማ ጥቅሞችን ለመጠየቅ በማጣቀሻነት ያገለግላል።
ለእንግሊዝ ዜጎች ዕድሜያቸው 16 ዓመት ሲሞላቸው NINO ይሰጣቸዋል። ለስደተኞችም NINO ይሰጣቸዋል። ሆኖም፣ ይህ ለእያንዳንዱ የመስራት መብት ላለው ሰው የማይሰራ በመሆኑ ለአንዱ ማመልከት ሊኖርብዎ ይችላል።
ያለ NINO ስራ ሊጀምሩ ይችላሉ ነገር ግን ብሔራዊ የመድን ዋስትና መዋጮዎችዎ እና የሚከፍሉት የግብር ክፍያ በትክክል በስምዎ መመዝገባቸውን ለማረጋገጥ አንዱ ሊኖርዎት ይገባል። ይህ እስከ 16 ሳምንታት ሊወስድ ስለሚችል በተቻለ ፍጥነት ይህን ማድረግ ጠቃሚ ነው።

 

የሰራተኛ እጥረት ዝርዝር

የሰራተኛ እጥረት ዝርዝር የዩኬ የንግድ ድርጅቶችና ቀጣሪዎችን የሰራተኞች እጥረት ያሉባቸው ስራዎችን የሚያሳይ ዝርዝር ነው።
ጥገኝነት የሚጠይቁ ሰዎች መስራት የማይፈቀድላቸው ቢሆንም ጥያቄያቸው ያለ ምንም የእነርሱ ስህተት ከ 12 ወራት በላይ መልስ የማያገኝ ከሆነና ብቁ ሆነው ከተገኙ በሰራተኛ እጥረት ዝርዝር ላይ ለተገለጹ ስራዎች ለማመልከት ብቁ ይሆናሉ።
እነዚህን ስራዎች የመስራት መብት ለማግኘት ለዩኬ ቪዛዎች እና ኢሚግሬሽን ማመልከት ይጠበቅብዎታል።

 

የማሳወቅና የማገድ አገልግሎት

በዩኬ ውስጥ ያሉ ብዙ ስራዎች የወንጀል መዝገብ የኋላ ታሪክ ማጣራትን ይጠይቃሉ። እነዚህ በአብዛኛው ከህጻናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኛ ሰዎች ጋር መስራትን ይይዛሉ።
የማሳወቅና የማገድ አገልግሎት (DBS) ቀጣሪዎችዎ የወንጀል መዝገብዎን የሚያጣሩበት ዘዴ ነው። ማጣሪያዎቹ የሚደረጉት በዩኬ ውስጥ ብቻ ነው። ባለፉት 5 ዓመታት ውስጥ ዩኬ ውስጥ ካልኖሩ ከትውልድ አገርዎ ‘የመልካም ሥነ ምግባር የምስክር ወረቀት’ እንዲሰጥዎ ማመልከት ሊኖርብዎ ይችላል። የማመልከቻ ሂደቱ ከአገር አገር ይለያያል።
እነዚህን መዝገቦች ከአገርዎ ማግኘት ሊከብድዎት ስለሚችል ቀጣሪዎችዎን እንደ ተጨማሪ የባህሪ የድጋፍ ደብዳቤዎች የመሳሰሉ አማራጭ ማጣሪያዎችን እንዲጠቀሙ ማነጋገርዎ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
በተጨማሪም በህግ ሙያተኛ ፊት የተሰጠ ‘ቃለ መኃላ’ ማቅረብ ይችላሉ።
አንዳንድ የወንጀል ፍርዶች ‘ያበቁ’ ተደርገው ስለሚወሰዱ መገለጽ አያስፈልጋቸውም። ሆኖም፣ ሕጎቹ ውስብስብ ስለሆኑ የወንጀል ፍርድ ካለብዎ ስለዚህ በቀጣሪዎ የሚጠየቁ ስለመሆኑ በተመለከተ ምክር ቢጠይቁ የተሻለ ነው።

ዋና ዋና ነጥቦች

1. ያለ ትክክለኛ ሰነድ ዩኬ ውስጥ መስራት ህገወጥ ነው
2. ቀጣሪዎች ለመስራት ብቁ መሆንዎን ለማረጋገጥ የማጋሪያ ኮድ መጠየቅ አለባቸው
3. ለመስራት ወይም ጥቅማ ጥቅሞችን ለመጠየቅ ለብሔራዊ የመድን ዋስትና ቁጥር ማመልከት አለብዎ
4. በዩኬ ውስጥ ያሉ ብዙ ስራዎች DBS ተብሎ የሚጠራውን የወንጀል መዝገብ የኋላ ታሪክ ማጣራትን ይጠይቃሉ።
Last updated: 23rd August 2023